Monday, April 25, 2016

<<ጉዳዩ>>

ማሳሰቢያ:– 35% ግነትና ቅጥፈት።

  • ለመንደራችን ሁለተኛ ለመኖሪያ ቤታችን አንደኛ የሆነው ዘመናዊ "ጉዳይ" ዛሬ  በወንድሞቼ ታጅቦ ከቤታችን ይደርሳል። ጉዳዩ ቤታችን እስኪደርስ ከጊቢያችን በር ላይ ከአቻ ጓደኞቼ ጋር ተሰብስበን በናፍቆትና በጭንቀት በመጠባበቅ ላይ ሳለን…

"አኩም አልጄጆን?(አሁንም አልደረሱም)?" የሚለው የሴት አያቴ ድምፅ ከግቢው ውስጥ ተሰማኝ። ይሄን ጥያቄ ለሰላሳ ምናምነኛ ጊዜ ስትጠይቀኝ ነው!!

ለአፍታ ዞሬ በተሰላቸ ድምፅ

"አልደረሱም!" አልኳትና አይኔን ወደ ወንድሞቼና "ጉዳዩ" መምጫ  ጎዳና መለስኩ። መዘግየታቸው ህሊናዬን በሊሆን ይችላል ስጋት አጨናንቆታል… ወረሱት ይሆን እንዴ? ወይስ መንገድ ላይ የሚመጡበት መኪና ጎማ ፈንድቶ ይሆን? እያልኩ በጣም ተወዛግቤያለው። የአያቴና የጓደኞቼ አሰልቺና ተደጋጋሚ ጥያቄ ደግሞ ከመጠበቁ በላይ አዛ ያደረገኝ ጉዳይ ነው። መጠባበቅ ቋቅ እስኪለኝ ያሰለቸኝ አንሶ! ይነዘንዙኛል… ኡፋህ…

• ዛሬ ከቤታችን ይደርሳል የተባለው ጉዳይ ከሁለት ወር በፊት ነበር… ጅዳ  የምትኖረው አክስታችን ደውላ…"ጉዳዩን ልኬላቹሃለው ከጉምሩክ ሲደውሉላችሁ ሄዳችሁ ተረከቡ" ብላ ለትልቁ ወንድሜ በጎረቤት ስልክ የነገረችው።  ይህን ዜና መጥቶ ሲነግረን በአያቴ እልልታ በእህቴ ጩኸት በእኔ ፉጨት ቤታችን የኢያሪኮን ከተማ መሰለች። ቤተሰቡ ይህን ዜና ከሰማ ቅፅበት ጀምሮ  ወሬው  ስለ ጉዳዩ… ጉዳዩ… ጉዳዩ ሆነ። (በተለይ!! የእኔና የአያቴ  ወሬ…)

አያቴ በቡና ሰአት ለተሰበሰቡ ጎረቤቶች ከቡናው ጀባታ ቀጥሎ  ወሬዋ ሁሉ ስለ ጉዳዩ ጉምሩክ መድረስና በቅርቡ ቤታችን እንደሚደርስ… ማብራራት ነበር

"ለእኔ ለእናቷ ደስታ ብላ! ላቧን አንጠፍጥፋ እቁብ ገብታ ባጠራቀመችው ብር …  ከፋብሪካው ልክ እደተመረተ በትኩስነቱ… በውድ ገዝታ… በቶሎ ይድረስላት ብላ በአየር እጥፍ ከፍላ ነው የላከችልኝ…ጉዳዩ ብርቅ የሆነበት ጎረቤትም ጭንቅላቱን በአግራሞት እየነቀነቀ ያዳምጣታል።

አያቴ ቡና እንድትደግምላት ለእህቴ ሲኒውን እያቀበለች ማብራሪያዋን ቀጠለች …" ሴት ልጅ ናት መልበስ ማጌጥ ያምራታል፣ ፍላጎቷን ትታ እኔ እናቷ ደስ እንዲለኝ ብላ …  የለቅሶ ሳግ ማብራሪያዋን አደናቀፋት …

"ይተዉ እንጂ እማማ ይተዉ! እሷስ ያለ እርሶ ማን አላት! ለርሶ ደስታ ምንስ ብታደርግ ይበዛብዎታል እንዴ ? እንደውም ሲያንስዎ…ነው! የተመረቀች ክፉ አይንካት! እንዳስደሰተችዎ አላህ በባል በልጅ ያስደስታት! እርስዎ ብቻ ዱዓ ያድርጉላት!! እንጂ ውለታዋ ሲያንስዎ" አሉ እትዬ ዙበይዳ አያቴን ለማረጋጋት።
"እሱስ ልክ ነው…በዱዓውማ መች አሰቀርቼባት አውቃለው! … አለች! አያቴ ውለታው እንደማይበዛባት እየተስማማችና አይኖቿ ላይ የተጋገረውን እንባዋን በመቅረቢያዋ እየጠረገች። ቀጠሉ ጋሽ ጀማል…

"አይ ወርቅ! እንደሷ አይነት አስር ቢወለድ አይቆጭም! የተመረቀች! አላህ የመረቃት! አለች እንጂ የኔ እንከፍ… " አሉ ያጋመሱትን ቡና ፉት እያሉለት።

"አለች…እንጂ የኔ እንከፍ! ለስሙ ከአገር የወጣችው ከሰው ሁሉ በፊት ነው። አንድ ቀን እንደ ሰው አንድቀን!… ወላ ለኔ ሆነ ወላ ለእናቷ አንድ ጠቃሚ ነገር ልካም አታውቅ!! እርግጥ ነው አልክድም ሳታቋርጥ አንድ የምትልክልን ነገር አለ ለኔም ሆነ ለናቷ…  ።"አሉና  የስኒ ቡናቸውን አንስተው አገገባደዱ።

"ገንዘብ ነው ሳታቋርጥ ምትልክልዎ ጋሽ ጀማል?" ጠየቁ እትዬ ዙቤይዳ።

"ትቀልጃለሽ ልበል ዙበይዳ?"

"ታዲያ ምንድነው?"

"ነጋ ጠባ የምትልክልኝ?"

"እህ… !" አሉ በህብረት ። የሰዉ ጆሮ ሁሉ ወደ መልሳቸው ተቀሰረ።

"ህእ …አሉ ጋሽ ጀማል…በሹፈት…

ህእ…  ነጋ ጠባ ከሷ የሚደርሰኝማ  ደብዳቤ ነው።  ዛሬም ደብዳቤ… ነገም ደብዳቤ… ደብዳቤ በልተን የምናድር ይመስል። አንዳንዴማ በቃ ስራዋ ሁሉ ደብዳቤ መፃፍ ብቻ ይመስለኛል! እኔም ሆንኩ እናቷ በዚህ እድሜያችን የሚያስፈልገን ጧሪ ቀባሪ እንጂ! የብዕር ጓደኛ ነው እንዴ?…ነው ወይ? ብለው ጋሽ ጀማል ታዳሚው ላይ በልጃቸው ንዴት አፈጠጡ…

" ጉድ እኮ ነው! ልጄ ባይልላት እንጂ! በኛስ አትጨክንም! እርሶ ደግሞ" አሉ ባለቤታቸው እትዬ አለማሽ።

"አረ! ባይልላት…ነው?ተይ እንጂ?  ወገኛ!! ሌላው ይቅር የምትፅፍበት የወረቀትና የእስክሪቢቶውን እንኳ ብትልክልን ምናለበት? ለስሙ ልጅ ውጪ አለቻቸው መባሉ አልቀረ!!  ይኸውላችሁ አሁንማ የምትልከው ደብዳቤ ብዛቱ… ቤቴን ከመኖሪያነት ወደ መዝገብ ቤትነት ቀይሮታል!" ቤታችን ሳቅ ሞላው።

•  የድምፁ ጩኸት ለመላ ጎረቤት የሚሰማው የጎረቤታችን ስልክ ቂርርርርር አያለ  በተንጫረረ ቁጥር ቤተሰቡ መለ አካሉ ጆሮ ይሆናል። ከጉምሩክ የተደወለ እየመሰለን ጆሮአችን እንደ ባለጌ ጣት ይቀሰራል!!
አንድ ቀን ሁላችንም በተሰበሰብንበት ይሄ መከረኛ ስልክ ጮኸ…
ካሁን አሁን… ሊጠሩን ነው … ከጉምሩክ ነው … በሚል ጉጉት ሁላችንም መርፌ ቢወድቅ በሚሰማ መልኩ ባለንበት ቀጥ ፀጥ ብለን… ስንጠብቅ። የጎረቤታችን በር ተከፈትና በስልክ የተፈለገው ሌላ ሰው ስም ተጠራ።

"ኤጭ! ይሄ ደግሞ ከመደዋወል ሌላ ስራ የለውም እንዴ!?" ብዬ የተደወለለትን ሰው በሆዴ ቦጨኩት። በቤተሰቡ ሰፍኖ የቆየው ፀጥታ አበቃና … ወሬው ጀመረ… ስለሚመጣው ጉዳይ…

"ቆይ መቼ ነው የሚደውሉት?" ብላ ትጠይቃለች ታላቄ።

"ያው እስኪደውሉ መጠበቅ ነው!" ይላል መካከለኛው ወንድሜ አሊ።

አያቴ በስጋት "ጉርሙኮች ንብረት ይወርሳሉ! የሚሉትስ?"  ወይኔ ልጄ ሁሉ ይቅርብኝ ብላ የላከቸውን ብቻ… ስጋቷን… ሳትጨርሰው… ወንድሜ ጣልቃ ገባና…

"የሚወርሱት "ጉዳዩን" ሳይሆን ቀረጥ ሳይከፈልባቸው የተወዘፉ እቃዎችንና እቃና የሺሻ እቃ ነው"።

"የምንሻሽ እቃ??" አለች አያቴ።

"የሺሻ እቃ!"

"ምን አፈርን ኡሃንጋ? (ምንድነው እሱ ደግሞ? "

  ወንድሜ የሺሻ እቃን ለአያቴ የሚያስረዳበት ቋንቋ አምጦ አምጦ! በመጨረሻም… "ገመድ በመሰለ ትቦ የሚጨስ ሲጃራ ነው…!"
አለ።

"ይሄ እነ ሩቂያ አረቧ አንዳንዴ የሚያጨሱበት ነገር ነው?" አልኩት።

አንተ ነገረ ፈጅ! በሚል ግልምጫ አየኝና "አዎ" አለ በተገላገልኩ ስሜት።

• በእንደዚህ አይነት ካሁን ካሁን ደወሉልን ጉጉት ሁለት ወር ካለፈ ቡሃላ … ትላንት ከጉምሩክ ተደወለና ወንድሜ መጥተህ ውሰድ ተባለ። ጉዳዩን ለማምጣት በሌሊት ጉምሩክ ሄደዋል ሁለት ታላላቅ ወንድሞቼ

"ምንድነው አይደርሱም እንዴ?" አለኝ አቻ ጓደኛዬ አብዱ።

"ካንተ ጋር አይደለው እንዴ ያለሁት ምን እኔን ትጠይቀኛለህ?" እየተነጫነጭኩ መለስኩለት።

"እነ ከድር ከሄዱ ቆዩ ግን?" ሌላው ጓዴ ጀማል። እኚህ ሰዎች! አብደው ሊያሳብዱኝ ነው እንዴ?

"ሌሊት ቆማጣ ሳያራ ነው የሄዱት አላልኩህም!እናትንና! ካሁን ቡሃላ ብዬ ደግመህ ብጠይቀኝ አይንህን ነው በኩርኩም ምልህ ጅል!።" ብዬ ከዛቻ ጋር መለስኩለት።

"እንዴ የጠየኩህ አልመሰለኝማ!?" እያለ አጉረመረመ።

"በቃ ዝም በል! ጅብ አንጎል!።

ጀማል የሚመጣውን ጉዳይ በቤታቸው እንዳላይ ማዕቀብ ይጥልብኛል ብሎ ሰጋ መሰለኝ መልስ ሳይጨምር ዝም አለ።

   • ጥበቃው አታክቶኝ ወደ ግቢ ገባው። ግቢ በገባው ከአፍታ ቆይታ ቡሃላ… ጓደኞቼ በጅምላ  ሰላም… ሰላም… እያሉ ጠሩኝ ። ጉ ዳዩ መድረሱን አወኩ። ተርርር ብዬ ወደ ውጪ ወጣው። ቮልክስዋገን ፒካኘ መኪና ወደ ሰፈሬ … ጠ… ጠ… ጠ… ጠ… አያለች… መጥታ ግቢ በራችን ላይ ቆመች። የሰፈሬ ጎረምሶች መኪናዋን በመክበብ የ"ጉዳዩን" ደህንነት ወደላይ ወደታች እየተገለማመጡ ይቆጣጠራሉ። በኛ ጫጫታ ጎረቤት ሁሉ ለ"ጉዳዩ" አቀባበል ለማድረግ ግልብጥ ብሎ ወጣ። በደህንነት ጠባቂ ጎረምሶች ምንም አስጊ ሁኔታ አለመኖሩን የተረጋገጠላቸው ሁለቱም ወንድሞቼ ከመኪናዋ ዱብ ዱብ እያሉ ወረዱ። እልልልል… የወይዛዝርት እልልታ መንደሬን ቀወጣት። አያቴ ልጇን እንደምትድር እናት ወገቧን አስራ ጉድ ጉድ ትላለች፣ እህቴ ለጉዳዩ ቤት ውስጥ ቦታ ታስተካክላች። አኔ ከጓደኞቼ ጋር የአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ በደስታ እንጫጫለን። "ጉዳዩን" ከመኪናው አውርዶ የወንድሞቼ መኝታ ክፍል ተሸክሞ ለማድረስ በፍትሃዊ ምርጫ … በድምፅ ብልጫ ከጎረምሶች ደንዳናው ተመረጠ። "ጉዳዩ" በተመራጭ ጎረምሳ መሀል አናት ተቀምጦ ጉዞ ጀመረ …  እኔና ጓደኞቼ ከጉዳዩ ከፊት ከፊት እየሄድን… "ዞር በሉ…መንገድ ልቀቁ!… መንገዱን ክፍት እናስደርጋለን።ከጉዳዩ ኋላ ተገልብጦ የወጣው ጎረቤት በደመቀ ሁኔታ አጅቦ ይከተላል።(የሁኔታው ድምቀት ታቦት ወደ ማደሪያው የሚሄድ እንጂ ጉዳዩ ወደቤታችን የሚገባ አይመስልም ነበር)። የሆነው ሆኖ ከአክስታችን የተላከው "ጉዳይ" ከሁለት ወር ጥበቃ ቡሃላ ቤታች ለመድረስ በቃ።

  • ከደማቁ የአቀባበል ስነስርአት ቡኃላ ጎረቤት ዘመድ አዝማድ ተበተነ። ጉዳዩም ከወንድሞቼ መኝታ ክፍል ተቀምጦ ተቆለፈበት። በትልቁ ቤት መላ ቤተሰቡ ተሰብስቦ በታላቅ ወንድሜ አፈ ጉባኤነት ስለ "ጉዳዩ" የአጠቃቀም በሁለቱም ወንድሞቼ የረቀቀው ህግና ደንብ ተነበበ። በወንድሞቼ ክፍል እንደሚያድር የተወሰነውን ጉዳይ ለማየት እኔና እህቴ በወንድሞቼ አልጋ ላይ ለአራት ለማደር ተገደድን። እንደዚህ በጉጉት በደማቅ በሀገር መሪ አቀባበል የተደረገለት፣እና ለማየት ጓጉተን አንድ አልጋ ላይ ለአራት ያስተኛን "ጉዳይ" ዛሬ ጊዜ ጥሎት እንደ ጠረጴዛ የመፅሀፍ መደርደሪያ ሆኗል…ጉዳዩ TOSHIBA እንጨት ለበስ  21" ባለ ቀለም TELEVISION ነበር።

No comments:

Post a Comment