Tuesday, April 5, 2016

ውርስ

☞ በሃገራችን የሚኖሩ የአረብ ክልስ አዛውንት ናቸው ። ሲበዛ ቀልደኛናተጫዋች ። ከወጣቱ ወጣት ከትልቁ ትልቅ ። ሁሉን እንደየ ደረጃው የሚግባቡ ። የአራት ወንድ ልጆች አባት ። በወጣትነት ዘመናቸው ቀልጣፋ ነጋዴ መሆናቸው የደረሱበት የዛሬው የሀብት መጠናቸው ማሳያ ነው ። እንደ ጥንቸል ሩጠው እንደ ጉንዳንታትረው ያካበቱት ድርጅትና ሀብት ዛሬ በእድሜ መግፋት ምክኒያት ሊቆጣጠሩት አልተቻላቸውም ለዚህም ነበር ልጆቻቸውን ሰብስበው ሀብታቸውን ለማካፈል የወሰኑት ። በእቅዳቸው መሰረት የነበራቸውን ሀብት ልጆቼ እንደ ቀድሞው ይንከባከቡኛል በማለት ለራሳቸው ድንቡሎ ሳያስቀሩ ጠቅላላ ለልጆቻቸው አከፋፈሉ ። …ቀናት ነጎዱ ወራት ሄዱ … ከልጆቼ አገኘዋለው ያሉት ተስፋ ያደረጉት እንክብካቤ የውሃ ሽታ ሆነ… ልጆቻቸው በራሳቸው ርዕዮተ አለም ሆነው አዛወንት አባታቸውን ዘነጉ… አዛውንት ይህ የልጆቻቸው ሁኔታ ነደዳቸው… አበሳጫቸው… የልጆቻቸውን እንክብካቤ መመለስ ሻቱ ። መላም ያሰላስሉ ጀመር… አሰላሰሉ …መላው መጣላቸው ። በዚህም መሰረት ልጆቻቸውን አንድ በአንድ ለየብቻ እየቀጠሩ እንዲህ አሉ… " ባለፈው ያካፈልኳችሁ የሀብቴን ግማሽ እጅ ነው ግማሹ እጅ ያስቀመጥኩት በወርቅ መልክ ነው እሱም የሚገኘው ከማዘወትራት መደቤ ስር ተቀብሮ ነው። ይህን የወርቅ ሀብት የማወርሰው ከልጆቼ ውስጥ ለኔ የተለየ እንክብካቤ ላደረገ ልጄ ነው ብዬ ለራሴ ቃል ገብቻለው ። ።ይህን ለወንድሞችህ አትንገር የማወርሰው ላንተ ነው ። ስለዚህ ቃሌም እንዳይታጠፍ ላንተም ለማውረስ ከወንድሞችህ በተለየ እንክብካቤ ታደርግልኛለህ!! በዚህ ከተስማማን ሀብቱ ያንተ ነው ። ማውጣትና መጠቀም የምትችለው ግን ከሞትኩ ቡሃላ ነው ። " በማለት ለአራቱም ለማንም አትንገር እያሉ ተናገሩ ። ከዛ ቡሃላማ በቃ አባት በልጆቻቸው እንክብካቤ ናላቸው እስኪዞር ሰከሩ ። ልጆቹም ሚስትና ልጆቻቸውን እስኪዘነጉ ድረስ ለአባታቸው የሚፈልጉትን ያለ ገደብ ያደርጉ ጀመር… አባት ተነፍገው የነበረው የልጆቻቸው እንክብካቤ ከጠበቁት በላይ ሆነ ። ጊዜያት ሄዱ ። የማይደርስ የለም ጊዜው ደረሰና አባት ሞቱ ። ሀዘንተኛው ተበታተነ ። ለወርቁ ውርስ ሲሉ አባታቸውን የተንከባከቡ አሳማ ልጆች ሚስጥሩን ለአንዳቸው ሳይነግሩ አባት ዘወትር ከሚቀመጡባት የአርማታ መደብ ስር ያንዣብቡ ገቡ ። ቢታይ ንቅንቅ የሚል ጠፋ ። በመጨረሻም አንዱ ደፍሮ ተናገረ ። አራቱም ለኔም ብሎኛል ለኔም ብሎኛል በማለት መደቡ አካባቢ እንደ በረሮ ያረመሰመሳቸውን ሚስጥር ተናዘዙ ። በዚህም መሰረት ወርቁን አብረው ለማውጣትና ለመካፈል ተስማሙ ። የአርማታው መደቡ ላይ የተነጠፈውን ምንጣፍ አነሱ ። እርግጥም አንዳች ነገር ተቆፍሮ እንደተቀበረ የሚያሳይ በሌላ የሲሚንቶ ልስን ተመለከቱ ። ሞራላቸው ጨመረ ። መቆፈር ጀመሩ ድርሻው ብዙ በቆፈረ ይመስል እየተስገበገቡ … ቆፈሩ… ቆፈሩ አፈሩን ቆለሉ… የዝሆን ጥርስ የሚያክል ቀንድ አገኙ … አወጡት። ቀንድ ነው… በግርምት ተያዩ… ድጋሚ ወደ ቀንዱ አዩ… ገጀራ በሚያክለው በቀንዱ ትቦ ውስጥ ተጠቅልሎ የተወተፈ ወረቀት ተመለከቱ አወጡት… ወረቀቱ ላይ የሰፈረው ከአባትነት ይልቅ ለውርስ በሚል መንከባከባቸው ያናደዳቸው የአባታቸው መልዕክት ነበር … ☞"በህይወት እያለ ሀብቱን ጨረሶ የሚካፍል …ቀንዱን የሚያክል… ይግባለት " የታባክ ምድረ ሆዳም!!

No comments:

Post a Comment