Tuesday, April 5, 2016

ከልጅነት የሸር ትውስታዎቼ


                  ★★★★★★★★★★★★★

   በመርካቶ አካባቢ ከአያቴ ጋር ባደኩበት የልጅነቴ ገጠመኜ ውስጥ ሁሌም ፈገግ የሚያሰኘኝን ለናንተ የፌስቡክ ጓዶቼ  አካፍላችሁ ዘንድ… ብዕሬን ከአፎቱ መዝዤ,,,,በማለት እንደ ደራሲ ለመሆን አይሰራራኝም ምክኒያቱም በሞባይል ኪቦርድ ነው የፃፍኩት ። ለማንኛውም በኪቦርድም ሆነ በጊታር ሀሳቤን ላካፍላችሁ,,,,

   በአካል የማውቃችሁ አቻ ጓደኞቼ (አዛ ነገር ናችሁ መቼም) አሁን ይህቺም ፅሁፍ ሆና በሽሙጥ :ፉገራ፣በትችትና፣በነቆራ እንደ ቃሪያ አቃጥላችሁ እንደ ቃሪያ እንደምታራግፉኝ አውቃለው,,, መቻያውን ይስጠኝ ብቻ,,,

ወደ ገጠመኜ,,,

   መኖሪያ ቤታች በጠቅላላ ሶስት ክፍሎች ሲሆኑ ከዋናው ቤታችን(ሳሎንም መኝታም) ፊት ለፊት ሁለቱ  ክፍሎች ይገኛሉ።  የቤታችንን አቀማመጥ ለተመለከተ ሰው ሁለቱ ክፍሎች ከትልቁ ቤት ሁሌም አፍ ለአፍ ገጥመው የሚማከሩ ሊመስለው ይችላል,,,(ይምሰለዋ!)።  መሀከላቸውን የሚያቋርጥ ቀጭን ጎረቤት አገናኝ የጋራ መንገድ አለ ,,,

  የቤታችን የተከበሩ ታላላቅ ቁሶች የሚገኘው ከትልቁ ቤት ሲሆን ሁለቱ ቤት የሚገኘው ኮልኮሌ ቁስ ነው። ተማሪ ሳለው ትምህርት የሌለ ጊዜ  ቤት ስውል ዋናው ቤት መዋል እወድ ነበር። ታዲያ ማልነካካው ነገር አልነበረም,,,በተለይ ያ! ግድንግድ እንጨት ለበስ ቶሺባ ቲቪ (ፈረደበት መቼም!!) ናሽናል ሬዲዮ,,, የድሮ ፎቶዎች,,, አቤት ኮተት,,, መነካካት ነው በቃ። በጊዜው ለሸር ንቁ የሆነ ቅልጥፍና ነበረኝ አሁን የት እንደገባ እንጃለቱ ። ምን ነበር ንቃቴ  ለትምህርት ቢሆን,,,ኖሮ,,, ምፅ!…

   አያቴ አርብ ቀን  መስጊድ የመዋል ልምድ ነበራት ረፋድ ላይ ሄዳ ማምሻው ላይ ትመጣ ነበር ። ኢስላማዊ ትምህርት ቤት እማር ስለነበር በዛን ቀን ትምህርት አይኖረንም ። ለሱ ማካካሻ ቅዳሜ እስከ 6:30 ያስተምሩን ነበር ። አርብ ለኔ የመነካካት ሱሴን ማስታግስበት ቀኔ ነው ። የአያቴን እግር ጠብቄ ቤቱን ምስቅልቅሉን
የማወጣበት ቀን ነው ። ምን እንደምፈልግ እንጃልኝ ብቻ። እናላችሁ አንድ አርብ ቀን ትዝ ይለኛል የአያቴን እግር ጠብቄ ከች ስል!  ያለወትሮው ትልቁ ቤት ተቆልፏል! ተናደድኩ ተበሳጨው!

ቆይ ባልሰራላት,,,!! አልኩና የሸር እቅድ አሰላሰልኩ,,, ነደፍኩ,,,በውጥኔ ፈገግ አልኩ,,,

  ቱርርር,,,, ብዬ ሱቅ ሄጄ ልሙጥ ወረቀት ገዛው! ሰፈራችን በጣም የምቀርበው ጅምላ ሱቅ የሚሰራ ትንሽ የሚበልጠኝ ልጅ ጋር ሄድኩና ልሙጡን ወረቀት ብዥ የሚል ማህተም እንዲኖረው ማህተም ደመቅ አድርገህ ምታልኝ አልኩት

"ለምን ፈልገከው ነው? " ኮስተር ብሎ

"ከት/ቤት እጅ ስራ ስሩ ተብለን ነው " አልኩት

መልሴ አልገባ ሲለውና እንዳልገባው ለማሳወቅ ስላልፈለገ ምንም ሰይለኝ እንዳልኩት ማህተሙን መታልኝ… በነካ እጄ ፓርከርም ተውሼው  ወደ ግቢ ገባው። ,,,ማንም እንዳያየኝ ግራ ቀኜን ገላምጬ,,, በፓርከሩ ወረቀቱ ላይ diagonal (ከታች ወደ ላይ  አግድም) በትልቁ ታሽጓል ብዬ ፃፍኩበት,,,

                                ል "
                      ጓ
             ሽ
"ታ

 
  ወረቀቱን በሩ ላይ ወስጄ ለጠፍኩት። ራቅ ብዬ ሁኔታውን ለመከታተል አይኔን ወደ በራችን  ወረወርኩ ። ትንሽ እንደቆየ የቤታችን በር ሬሳ እንደሚወጣበት ቤት በሩ ላይ  ፊቱን በሀዘን የከሰከሰ፣እጆቹን በደረቱ አጣምሮ ጭንቅላቱን  ወደ ትከሻው የቀበረ,,,ብቻ ብዙ ሰዎች ተገጠገጠ ,,,የሚሉትን ለመስማት ጠጋ አልኩ,,,ሰዎቹ ቤቱ በቀበሌ  የታሸገበትን ምክኒያት መላምት እውነት አድርገው  ይቀዳሉ,, " እኔ እሰማለው,,, ወደ ጆሮዬ ከሚገቡ የወሬ ግንጣዮች ውስጥ…

"የረጅም አመት የቤት ክራይ አልከፈሉም አሉ!" (አቤት መቀደድ!ወር በገባ ነው ምትከፍለው! እኔ በሆዴ)።

"ባፈው መታወቂያ ሊያድሱ ሄደው ተሳድበው ነበር አሉ "(ያ ሰላም!  ከየት አምጥቶ ነው ሰው ዝም ብሎ ሚዘረጠጠው!)

"የት ሄደው ነው ይህ ሁሉ ሲሆን? "

"ዛሬ አርብ አይደል መስጊድ ናቸው!"

"አሁን ሲመጡ ምን ይባላል?!በድጋጤ ፍንግል እንዳይሉ ብቻ! "
(አረ እራስሽ ፍንግል በይ!ሙሲባ! ሟርተኛ!)

ይህን መሰል ቅጥፈት አዘል መላምት ከግራ ቀኝ ሲናፈሱና በውስጤ የመልስ ምት ስሰጥ ቆየው ። የመጨረሻዋ አባባል ግን ትንሿ ልቤን ትንጠው ጀመር,,,

"አሁን ሲመጡ ምን ይባላል?!በድጋጤ ፍንግል እንዳይሉ ብቻ! " የምትለዋ ።

እውነት ስትመጣ በድንጋጤ የሆነ ነገር ብትሆንስ ? አልኩ
ጨነቀኝ፣ሰጋው፣ተርበተበትኩ,,,ምንም ቢሆን ነብስ ሳላውቅ ጀምሮ አሳድጋኛለች! ለዛውም በፍቅር፣በእዝነት፣ ,,, ይህን ይህን ሳሰላስል ለአያቴ ያለኝ ፍቅር ከውስጤ ተላውሶ ገነፈለብኝ  ወደ ለጠፍኩት ወረቀት ገፍትሮ አስሮጠኝ,,, ወረቀቱን ገነጠልኩና,,, እግሬ አውጪኝ ብዬ ተፈተለኩ,,,ከጀርባዬ የሚርቀኝ የሰዉ ስድብና እርግማን  ተከተለኝ ።

ከጊቢ እንደወጣው አንዱ የሰፈራችን ሰው  ጠርቶ የሆነ መልክት ሩቅ ቦታ እንዳደርስለት የታክሲ ሰጥቶ ላከኝ ። እኔም የሰራሁትን ለማስረሳት ከአካባቢው ዞር ማለቱን መርጬ  ያለወትሮዬ ፈጥኜ እሺ አልኩት ።

መልክቱን በታክሲ ተሳፈርኩ,,, በታክሲው ውስጥ

ሁለት ሴቶች የሞቀ ሀሜትና ወሬ ይዘዋል,,,ሳልፈልግ ወሬያቸው ከጆሮዬ ይጠልቅ ጀመር,,,

"ባለቤትሽ ተሻለው? መጥቼ እጠይቀዋለው ብዬ እንደው
አልሞላልሽ ብሎኝ እኮ ነው!! "

"መች ይሞላል ብለሽ ነው!! አዎ አሁን እሱ የተመሰገነ ይሁን ተነስቷል ስራም ጀምሯል!"

"እሰይ! እንደው ምን ይሳነዋል! ማንም ይተርፋል አላለም ነበር።
መንታ ልጆችሽስ? ደህና ናቸው? "

"ደህና ናቸው ምን ይሆናሉ ብለሽ ነው? አቃጠሉኝ እንጂ!!"

"ምነው ያስቸግራሉ? "

"አረ ተዩኝ እቴ! የነሱን ነገር እንደው እሱ አንድ መለያ ምልክት ካልሰጠኝ ሊገድሉኝ ነው!! 

" መቼም እንደ ምታውቂው እንደ አህያ አመሳስሎ የፈጠራቸው ጉዶች ናቸው ። እኔም የወለድኳቸው እንኳ መለየት እስኪሳነኝ አመሳስሏቸዋል። ነገሩ በመልክ ይመሳሰሉ እንጂ። በአበላልና በፀባይ አይገናኙም,,,እንደ እሳትና ውሃ፣ እንደ ነጭና ጥቁር፣ የተቃረነ ነው። ታላቅየው የወጣለት ተደባዳቢ ነገረኛ ሲሆን ያኛው ደግሞ ሰው ቀና ብሎ ማያይ ቀኙን ቢመቱት ግራውን የሚሰጥ ምስኪን ነው ።

"ተመስገን ብሎ! እንደ ፀባያቸው  መቻል ነው እንጂ!"
አለቻት ሳቅ እያለች,,,

"እሱማ ልክ ነሽ! እየውልሽ አንድ ጊዜ ያ ነገረኛው ትምህርት ቀርቶ,,, ከታች ሰፈር ልጆች በቡድን ይደባደብልሽና አምልጦ ወደ ቤት ይመጣልሻል ። ሚስኪኑ መንትያ ወንድሙ ከትምህርት ቤት አገር ሰላም ብሎ ሲመጣልሽ የታች ሰፈር ልጆች አግኝተውት,,,ከብብቱና ከምላሱ በቀር አካሉን በሙሉ  እንዳይሞት እንዳይተርፍ  አድርገው  ቀጥቅጠውት አይኑ  አብጦ፣ ፊቱ ተለውጦ መጣ  እልሻለው ።
ተመቶ ያበጠው ሚስኪኑ መሆኑ ነደደኝ እንጂ እብጠቱ አንዳቸውን ካንዳቸው ለመለየት ጠቅሞኝ ነበር ።

" ውይ እኔ እናቱን ይድፋኝ!! ምን ጨካኞች ናቸው እቴ! አንድ አይነት መሆናቸው የእግዜርን ተዓምር ከማሳየቱ በላይ ጉዳቱ እዚህ ጋር ነው ። ምን ይደረጋል መቼም!!

"ጠላትሽን!,,, ታዲያ የዚህ ጉደኛ ነገር መች ያልቃል ብለሽ,,,ወንድሙን በየ መንገዱ ያስደበደው መች በቅቶት,,,የወንድሙን ፋንታ ይበላበታል!! ጉድ እኮ ነው ሆዴ ውስጥ ሳሉ የወንድሙን ጨጓራ ደርቦ ይወለድ አላውቅም ብቻ ምንም በልቶ የሚጠግብ ጉድ አይደለም !!  መቼ ለታ ይሄ ጉደኛ መጥቶ  ምሳውን በልቶ ወጣ ። ትንሽ ቆይቶ ቲሸርት ቀይሮ ወንድሙ ሆኖ መጣና በላ ። እኔ አገር ሰላም ነው ብዬ በተቀመጥኩበት ይሄው ጉደኛ እያለቀሰ መጣ "ምነው " ስለው ተስፍሽ እንደኔ ገብቶ ምሳዬን እንደበላብኝ ነገረኝ " ብሎ አኩርፎ ቁጭ አለ,,,"የእናት ሆዴ አላስችል ብሎኝ አንስቼ ሰጠሁት!

የሚገርምሽ ሶስቱንም ጊዜ ልብሱንና ፀባዩን እየቀያየረ የበላው ያ ጉደኛ ተንኮለኛው ነው!! በዚህ ኑሮ ሶስቴ እየበላ እንኳን የኔን የሀገራችንን ኢኮኖሚ አያናጋም ትያለሽ? "

አብራት የነበረችው ሴትዮ አላስቻላትም ሷቋን አፈነዳችው,,,እኔም አጀብኳት,,,, ካካካካ ተባብረን የሚኒባሷን ጣራ ያርገበገበ ሳቅ አስካካን ። ወደራሴ ተመለስኩ  ለካ ከኔም የባሰ እሳት አለ ብዬ ሳቅኩ ከሱ አንፃር እኔ ጨዋ ነኝ አልኩ በሆዴ ።

ከተላኩበት  ወደ ቤት ስመለስ,,, አያቴ ከመስጂድ  መጥታ ቤታችን ቡና ፈልቶ፣ድንች ተቀቅሎ ,,,የቤቱ ድባብ ሞቆ አሸብርቆ ,,,የሰራሁትን ሸር እየተሳሳቁ ሲነግሯት እሷም በግርምት እየሳቀች ደረስኩ ።

"ይኸው መጣ ይህ ጉደኛ!አሉ አንዷ ጎረቤታችን እየሳቀች "

እኔን ሲያዩ ሁሉም በግርምት ሳቁ,,,

የኔ እንዲህ ያሳቃችሁ የመንትዮቹን ብትሰሙ ምን ልትሉ ኖሯል?" አልኩ በሆዴ ።

አያቴን ሳምኩና አጠገቧ ተቀመጥኩ ሳቅ የፈጠረው ድርጊቴም የዛን ለት ሳያስገርፈኝ አለፈ።

አስከዛሬ ድረስ ከሚያስቁኝ ገጠመኞቼ አንዱ ሆኗል ።

No comments:

Post a Comment