Monday, May 16, 2016

መርከዝ

ቅድም ከቀኑ 10:00 ቡኋላ ሰፈር ስጋ ቤት በር ላይ ተቀምጬ ሳለ። ስጋ ቤት የሚሰራ አንድ ልጅ ያለሁበት መጥቶ በስሜ ጠራኝና…

"ገና ከታች ሲመጡ ስታይ በኮድ ትነግረኛለህ…እደበቃለው!" አለኝ ስጋት በሚነበብት ገፅታ…

"ማንን?"

" የዳዕዋ ጀመዓዎችን ነዋ።"

ለምን? ብዬ አልጠየኩትም። የዳዕዋጀመዓ ልጆችን የሰጋበትን ምክኒያት እኔም ሆንኩ ሌሎች ሰዎችንም ገና ከሩቅ እንዳዩዋቸው የሚሸሹት ለምን እንደሆነ ምክኒያቱን ጠንቅቄ አውቀዋለው። እነሱ ግን ከሁኔታቸው እንደምረዳው ስጋት የፈጠሩበትን አመክንዮ የሚያውቁ አይመስለኝም። ቢያውቁ እስከዛሬ የሆነ መፍትሔ እንደሚያደርጉ አልጠራጠርም። ምክኒያቱን እነሱ አያውቁም እኛ እናውቃለን። ጆሮ ለራሱ ባዳ ነው ይባል የለ…

በሀጂ ሙሳ(ረሂመሁላህ) ነበር ለ3፣ ለ40 እና ለ120 ቀናት በመስጂድ ቆይታ የሀይማኖት ትምህርት የሚሰጥበትን አሠራር በሀገራችን መሰረቱ የተጣለው። ሀይማኖታዊ አስተምህሮ የሚሰጥበት ይህ የዳዕዋ ስራ መዓከላዊነቱ መርከዝ (ሀጂ ዘይኑ መስጊድ)ሲሆን ከተለያዩ ስፍራዎች ለትምህርቱ የመጡ ሰዎችን በቡድን ቡድን በማቀናጀት ወደ ተለያዩ የከተማና የክልል መስጂዶች አንድ መሪ (አሚር) እየተመደበላቸው ይላካሉ። ሰዎቹም ለፈቀዱት ቀን በተመደቡበት መስጂዶች በወንድማዊ ስሜት፣ ምግባቸውን እራሳቸው በየፈረቃ እየሰሩ፣ ከምንም አይነት ዓለማዊ ግንኙነት ታቅበው ሀይማኖታዊ ትምህር ብቻ  ይማማሩበታል፣እውቀት ያዳብሩበታል በተግባር ያውሉታል። ትምህሩቱን ጨርሰው ወደ መደበኛው ህይወታቸው በሚመለሱበት ወቅትም ከቀድሞው የተሻለ ስብዕና ይላበሳሉ። ይህን ድንቅ ለውጥ በራሴም ላይ የማውቀው ሲሆን እጅግ በጣም በአስቸጋሪነታቸው የሚታወቁ ወጣቶችንም አንደ ለወጠ አውቃለው። ትላንት ለህብረተሰቡ በእኩይ ድርጊታቸው አስጊ የነበሩ ወጣቶች በዚህ ዳዕዋ ሰበብ ዛሬ ተለውጠውና የመልካም ስነምግባር ባልተቤቶች ሆነው የህብረተሰቡ የሀይማኖት አስተማሪ ብሎም የመልካም ተግባራት አስታዋሽ አድርጓቸዋል። የሀይማኖት ፍላጎቱ እስከዚህም የነበረው ማህበረሰብ በዚሁ ሰበብ የሀይማኖት ንቃትን ፈጥሯል። የዚህን ዳዕዋ ጥቅም ብዘረዝረው ሙሉ መፅሀፍ አይበቃኝም። ከዚህ ዳዕዋ ጋር ተያይዞ በመንደሬ ውስጥ በአስታዋሽ ወንድሞቻችን በየቤታችን እየዞሩ ለአጭር ደቂቃ በመስጂድ ውስጥ በሚደረገው ትምህርት ላይ እንድንሳተፍ ጥሪ ያደርጉልናል።

  በተለይ እሁድ ከ10:00 ሰአት ቡሃላ በዚህ ጥሪ ላይ በአስታዋሽ ወንድሞች የሚደረገው ጥሪ መልካም እንደሆነ ሁሉ… በመጥራት ሂደታቸው የሚያደርጉት ጫና በርካታ ሰዎችን ከሩቅ እንዲሸሻቸው አድርጓል። የተሰበሰቡ ሰዎች ከሩቅ መምጣታቸውን ሲያዩ አድማ በታኝ ሀይል እንደመጣባቸው ሲበታተኑ እሁድ እሁድ የማየው ትዕይንት ተደጋጋሚ ነው።

• ቆይ ለመሆኑ መልካም ስራ የተሰማሩ ወጣቶችን ገና ስታዩ እንድትሸሹ ያደረገው ምንድነው? የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ ስለማውቅ በራሴው ገጠመኝ ላብራራው…

አንድ እሁድ ቀን በዚሁ ሰዓት የዳዕዋ ጥሪ አድራጊ ወጣቶች አገኙኝና ጥሪ አደረጉልኝ። ያልጨረስኩት ስራ ስላለ ጨርሼ እመጣለው አልኩ። አላመኑኝም!! አስር ደቂቃ ብቻ ነው! ብዙ አትቆይም! በመሳሰሉ ንግግሮች … ከአሰልቺ ክርክር ቡሃላ ሳላምንበት በይሉኝታ ጫና እሺ አሰኙኝ። እጄን ይዞ መስጊድ የሚያደርሰኝንም ሰው መደቡልኝ። አረ ግድ የለም እራሴው እሄዳለው ብልም ሰሚ አላገኘሁም። በሀይማኖት መልኩ ስለመጡብኝ እንጂ በሌላ ጉዳይ ቢሆን እንደኔ ፀባይ ተሳድቤያለው ወይ ተደባድቤያለው። አማራጩ ስላልነበረኝ እንደ እስረኛ በመደቡልኝ ጠባቂ መስጂድ ተወሰድኩ። በጠባቂ ታጅቤ መሄዴ የፈጠረብኝ ያለመታመን የስዕብና ጫና እንዳለ ሆኖ ያልጨረስኩት አጣዳፊ ስራ ላይ ልቤን ትቼ ስለመጣው የሚሰጠውን ትምህርት በቅጡ ሳልሰማ ተመለስኩ።

ከዛ ቡሃላ ጥሪ አድራጊ ጀመዓዎችን ከሩቅ ስመለከት የሚገጥመኝን ክርክር፣ እመጣለው ብልም እንደማያምኑኝ እያሰብኩ ከመልካም ስራቸው ሳልፈልግ መሸሽ ጀመርኩ። እንደውም አንድ ቀን ከጓደኛዬ ጋር ቤት በተቀመጥኩበት ከደጅ ድምፃቸውን ስሰማ ሌላ ሰው የለም በል! ብዬው ተከናንቤ ተኛው። ጓደኛዬም ከአሰልቺ ክርክር ቡሃላ ተረታና ሄደ። ከዛ ቡሃላ እኔ ላይ የተፈጠረው ስሜት በጓደኛዬም ላይ ተፈጠረ። እኛ ብቻ አይደለንም። በቤቱ ቁጭ ብሎ የዳዕዋ ጀመዓ አድራጊ ወንድሞች ሲመጡ "የለም በሉ!" የሚለውን ሰው ቤቱ ይቁጠረው። በሰፈሬ ማህበረሰብ የተፈጠረው ሽሽት በዚሁ ሳያቁት በፈጠሩት ሰበብ እንጂ በሌላ አይደለም።

እርግጥ ነው ተግባሩ ወደ መልካም ስራ የሚያደርስ መንገድ ነው ሊኮነን አይገባም። እንኔም አየኮነንኩ አይደለም። ብዙ አስቸጋሪ ልጆችን የተቀየረ፣ የህብረተሰቡን የሀይማኖት ስሜትን  ያነቃቃ ተግባር ነው አልክድም። ነገር ግን በጥሪው ሂደት የሚደረጉ አንዳንድ ተግባሮች ግቡ ኢላማዉን እንዳይመታ ያደርጉታል። እኔ የዳዕዋ አስታዋሽ ወንድሞቼን ይህን ይህን አድርጉ የማለት እውቀቱ የለኝም። ነገር ግን በጥሪ ሂደታቸው የሚያደርጉት በይሉኝታ አስሮ ያለፍላጎት በአድራሽ ወደ መስጂድ የመላኩ ዘይቤ ብዙውን ሰዉ እያሸሸው እንደሆነ እንዲያውቁ እፈልጋለው። ያለፍላጎት በይሉኝታ ጫና የሰበሰብነው ሰው በስርዓቱ ትምህርቱን ቀስሞ ተግባራዊ ተግባራዊ ያደርገዋል ማለት አስቸጋሪ ነው። አሁንም ዛሬም ነገም በዳዕዋ ተግባራቸው እንዲገፉበትም እሻለው። ቢሆንም ለተሻለ ውጤት መለወጥ ያለባቸውን ዘይቤ ለውጠው ቢሰማሩ መልካም ይመስለኛል። ጥሪውን በማስታወስ ብቻ ቢወስኑት፣ የይሉኝታ ጫና ባይፈጥሩበት፣ ያለፍላጎቱ በይሉኝታ እንዲሄድ ባያደርጉት… ለነሱ ያለው እሳቤና የመሸሽ አባዜ እንዲተው ያስገድደዋል ባይ ነኝ። ካጠፋው አፉ በሉኝ።

No comments:

Post a Comment