Friday, May 6, 2016

የ4ተኛ ክፍል ትውስታ

የ4ተኛ ክፍል የት/ት ዘመኔ እንደተጠናቀቀ ትምህርት ቤቴ ሁሉም ተማሪዎችና ወላጆች በተገኙበት የሰርትክፌትና በትምህርታቸው በደረጃ ለወጡ ተማሪዎች ሽልማት የሚሰጥበት ፕሮግራም አዘጋጀ። ምንም እንኳን እኔ በደረጃ ወጥተው በመሸለም ወላጆቻቸውን እንደሚያስደስቱ ተማሪዎች ደስታ ባልፈጥርላትም ሴት አያቴን ይዤ ኘሮግራሙ ላይ ተገኘው። እንደ ሀብታም ሰርግ የዘነጡ ታዳሚያን የኘሮግራሙን ድባብ አድምቀውታል። ከአፍታ ቆይታ ቡሃላ ዝግጅቱ ጀመረ። ቅድሚያ በተማሪ ድምፅ የተመረጡ የአመቱ ምርጥ አስተማሪዎች ተሸለሙ።ቀጥሎ አመቱን ሙሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የት/ት ቤታችንን ድንበር በማስከበር ረገድ ሚና የተጫወቱት የጥበቃ ሰራተኛው ጋሽ ሙስጤ ተሸለሙ። በማስከተል ከ6ተኛ ክፍል እስከ ዜሮ ክፍል በደረጃ የወጡ ተማሪዎች ተሸለሙ። ተሸላሚ ተማሪዎች ከወላጆቻቸው ከከባድ ጭብጨባ አንስቶ እስከ ከባድ ምርቃት ተቸራቸው። አያቴ ለኔ ማጨብጨብ ባያድላትም ለተሸለሙ ተማሪዎች ከማጨብጨብና ከመመረቅ አልቦዘነችም።

እኔ በአያቴ እግሮች መሀል ወንበር ተጋርቻች ተቀምጫለው። ሁኔታውን እታዘባለው። በዚህ መሃል አያቴን ዞር ብዬ አየኋት "ምነው አንተም እንደነዚህ ልጆች በተሸለምክልኝ!" በሚል አስተያየት ገረመመችኝ። እኔም ባሳየቺኝ የፊት ገፅታ ሀሳቧ ስለገባኝ በእፍረት አይኔን ወደ መድረኩ አሸሸው። መድረኩ ላይ ከነበረው ጠረጴዛ ላይ ለተሸላሚዎች በብልጭልጭ ወረቀት ታሽገው ከተዘጋጁ ስጦታዎች ውስጥ ሁሉም ታድሎ ሁለት ብቻ ቀርቷል። መድረኩ ላይ ፀጥታ ሰፈነ። የመድረኩን ፀጥታ ተከትሎ ታዳሚውም መርፌ ቢወድቅ እስኪሰማ ድረስ ፀጥ አለ። ተሸላሚ ተማሪዎችና ወላጆችን ጨምሮ ሁሉም ትኩረቱ የቀሩ ሁለት ስጦታዎች ላይ ሆነ።ቀሪ ሽልማቶች ለማን? እና በምን? በሚል ጉጉት ይከታተላል።

   የትምህርት ቤታችን ባለቤትና ዳይሬክተር ሙሂዲን እጅግ በጣም
በሚያምረው የወጣት ተክለ ቁመናው ጋር ከለበሰው ብራማ መሉ ሱፍ
አምሮ ከወትሮው በተለየ ግርማ ሞገስ ደምቋል። ሙሂዲን በእጁ
የምስክር ወረቀት ይዞ የደስታና የእርካታ ስሜት ፊቱ ላይ እየተነበበት
በታዳሚው ፀጥታ ውስጥ ኮቴው ቋ,,, ቋ,,, ቋ,,, እያደረገ ወደ መድረክ ሲወጣ የበለጠ ትኩረትን ሳበ። ከኮቴው ሪትም ጋር የታዳሚው የልብ ምት እኩል የደቃ(መሰለኝ)። ዳየሬከተር ሙሂዲን መድረኩ ላይ ተሰይሞ በሰላት ዙሪያ ንግግር አደረገ። ሶላቱ ያማረ ሰው ሁሉ ነገሩ የሚያምርለት እንደሆነ በውብ ፈገግታና ለዛ ለታዳሚው ዘከረ። ሀይማኖታዊ ትምህርት ቤት እንደመሆኑ መጠን ስለ ሀይማኖታዊ አምልኮና ስርአቶች ቦታ ሰጥቶ መግለፁ የሚጠበቅ ነበር። በመቀጠል የቀሩት ሁለት ልዮ ተሸላሚዎች
ከትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ሁሉ በሰላታቸው ሁሌም ከጀመዓ የማይጠፉ  ለሁለት የ4ተኛ ክፍል ተማሪዎች እንደሆነ ገለፀ። ታዳሚው ሁላ ከቀድሞው በበለጠ ጉጉት ሁለቱን በሰላት የሚሸለሙ ተማሪዎችን ለማየት አንገቱን አሰግስጎ ይጠብቅ ጀመር ።

ቲቸር ሙሂዲን ቀጠለ… እነዚህን ተማሪዎች እንዲሸልሙለት
የኑር መስጂድን ኢማም ወደ መድረኩ ጋበዘ

,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,, በሚለው ጭብጨባ ታጅበው ኢማሙም መድረኩ ላይ ተሰየሙ ።

ቲችር ሙሂዲን ቀጠለ,,,

★"በፈትህ ትምህርት ቤት በ1991 ዓ,ም በትምርት አመት
ከተማሪዎች ሁሉ በሰላት ተሸላሚ ተማሪዎች የሆኑት
"አብዱጀሊል መሀመድ ና አብዱሰላም ያሲን!" አለ በጎላ ድምፅ።

ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,, ,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ, ጭብጨባው

ከመድረኩ የተጠሩት ስሞች በጣም የምወደውና ምንን የማንለያየው
ጓደኛዬ የአብዱጀሊልና የእኔ ስም ነበር። በድንጋጤ ወደ አያቴ ዞሬ
ተያየን ደነገጥኩ።

እርግጥ ነው እኔና አብዱል ጀሊል በት/ቤቱ ግቢ ውስጥ ባለው መስጂድ ጀመዓ ሰላት እንደማያመልጠን ባውቅም እንደዚህ በወላጆቻችን መሀል ያሸልመኛል ብዬ አልጠበኩም።

በቅርብ ርቀት ተቀምጦ የነበረው ጓደኛዬ አብዱጀሊል መጣና "አብዱሴ እኛን እኮ ነው? እንሂድ እንጂ? " ብሎ እጄን ይዞ ወደ መድረኩ ጎተተኝ እኔም እጁን እንደያዝኩት ተከተልኩት። ያጀበን ጭብጨባና የወላጆች ከአንጀት የሆነ
ምርቃት መግለፅ ከምችለው በላይ ነበር።

መድረኩ ላይ ወጣን ኢማሙና ዳይሬክተር ሙሂዲን እየተቀባበሉ አገላብጠው እየሳሙ ሽልማታችንን ሰጡን። የወላጆች ጭብጨባና የደስታ ስሜት አየለ።

,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,, ,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,, ቿ,,,

ሽልማቱን ተቀብዬ መድረኩ ላይ ቆምኩ። ያሁሉ ሰው አይኑ እኔና ጓደኛዬ አ/ጀሊል ላይ ሆነ። ይሄ ሁሉ አይን በአንዴ አይቶኝ ስለማያውቅ መሰለኝ በጣም አሳፈረኝ። ቢጨንቀኝ አይኔን ወደ እማዬ መቀመጫ ወረወርኩት።  እማዬ በዙሪያዋ ካሉ ወላጆች ከሚደርሳት የእንኳን ደስያለሽ መልካም ምኞት ወከባ ውስጥ፣ሆና አይን ለአይን ተገጣጠምን። በከፍተኛ ደስታ አየሳቀችና እያነባች፣ በስስት ታየኛለች። የደስታዋን ሁኔታ ሳይ ዉስጤ የደስታ ይሁን የሀዘን ስሜት አንጀቴ ተላወሰ። ከመድረኩ በፍጥነት ወደሷ ሮጥኩ፣አጠገቧ እስክደርስ ናፈቀችኝ፣መንገዱ ራቀብኝ፣ ወላጆች አየያዙ ይስሙኛል፣ እንደምንም የሰውን መሰናክል አልፌ አጠገቧ ደረስኩ። የሆነ ሀይል እኔን የሚነጥቃት በሚመስል ፍጥነት ተንሰፍስፋ እቅፏ ውስጥ አኖረችኝ። ከንፈሬን፣ጉንጬን፣አንገቴን፣ አገጬን በፍቅር ሳመቺኝ። አያቴ ሊፒስቲክ አለመቀባቷ በጀኝ! ተቀብታ ቢሆን ኖሮ በአሳሳሟ ብቻ ፊቴ የቻይናን ባንዲራ ይመስል ነበር። እንዳቀፈች በደስታ አነባች። ታዳሚዎች ወደኔና ወደ አያቴ እየመጡ ዱአና በእንኳን ደስ አላችሁ ስሜት ከበቡን። ከኔና ከአብዱጀሊል ሽልማት ቡሃላ የእለቱ ኘሮግራም ተጠናቀቀ። ይህ ቀን በህይወቴ ትውስታው ከማይጠፋና መቼም ከማልረሳቸው ቀኖች አንዱ ነበር።

እማ ሁሌም ወድሻለው!! አላህ የጀነትም ያድርግሽ!!

No comments:

Post a Comment