Saturday, May 14, 2016

ረመዳን በድሮ መርካቶ

#ሳteናw
  ረመዳን ደረሰ አልሀምዱሊላህ ከዚህ ወር ጋር በተያያዘ ልጅ እያለው በሰፈሬ ላይ የነበረው ድባብ ዛሬም ድረስ ከሚተታወሱኝ የልጅነት ትውስታዎቼ አንዱ ነው ላክፍላችሁ…

የረመዳን ወር ሙስሊም በሆነና በቻለ ላይ ሁሉ የመፆም ግዴታ ነው። ወሩ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ ፣የፆም፣ የዱዓ፣ የሰላት፣ የዚክር ፣ የእዝነት፣የፍቅር ፣የሰላም ድባብ ከምንጊዜውም በላይ የሚልቅበት ወር ነው። መለኮታዎ መመሪያችን የሆነው ቁርዐንም የወረደው በዚሁ ወር ላይ ነው።
ወደ ትውስታዬ…

በመርካቶ ክልል ያደኩበት ሰፈር ስጋ ተራ ይባላል። በመርካቶ ገበያ ክልል ውስጥ አንድ አይነት ዕቃ በአንድ ስፍራ ውስጥ እንደሚገኙ ሁሉ የስፍራውም ስያሜ በዕቃው አይነት የተሰየመ ነው። ኮርቻ ተራ፣ ጫት ተራ፣ ሚሊተሪ ተራ፣ ጆንያ ተራ፣ ጋዝ ተራ፣ ቄጠማ ተራ፣ሎሚ ተራ፣ ጎማ ተራ በርበሬ … ተራ ዕቃዎቹ በብዛት የሚገኙባቸውን ስፍራ ናቸው። እንደዛ ስልህ ቦንብ ተራ ቦንብ በብዛት የሚገበይበት መስሎህ እንዳትሸወድ ባይሆን ቦንብ የሆኑ ነጋዴዎች ስለነበሩበት ከዛ የመጣ ስያሜ ነው። ሰፈሬ ኩታ ገጠም በሆኑት በስጋ ተራና በጫት ተራ አማካይ ስፍራ ነው። ስጋ ቤቶችና ጫት ቤቶች የከበቡት። ስለሆነም የኛ ሰፈር ማህበረ ሰብ ለጫትና ለስጋ እጅግ ቅርብ ስለነበር እንደ ስጋ ተጠቃሚው ባይሆንም የቃሚው ቁጥር ከፍተኛ ነበር። በፐርሰንቴጅ ስናወጣው የሰፈሬ ሰው 65 % የሚሆነው ቃሚ ነበር።

  ረመዳን ፆም በጫት ቃሚና በማይቅመው እኩል ተፅንዖ አያሳድርም። ከሱስ ነፃ የሆነ ሰው ፆሙ ቅልል እንደሚለው ሁሉ በቃሚው ላይ ፆሙ ቁልል ይሆንበት ነበር። ቃሚ መቃም ባስለመደበት ሰዓት ከመቃሙ በፊት ያለው ጊዜ "ሀራራ" ይሰኛል። ስሙን ከቃሚዎቹ ጊዜያዊ ስብዕናቸው ጋር በapproxmitly ስናጠጋጋው "ሀራሪስት" የሚል ስያሜ ይላበሳሉ። ሀራራ ቃሉ የተገኘው ከሀረር ይመስላል። ለማንኛውም ሀራራ ዘወትር ያስለመድከውን ሱስ ስታቐርጥ የሚፈጠር ተፅንዖ ማለት ነው። ታዲያ ይህ ወር ሲመጣ የሰፈሬ ሀራሪስቶች መግቢያ እንዳጣች አይጥ ይውተረተራሉ። ክተት የታወጀ ይመስል ይጨነቃሉ ይጠበባሉ። መጨነቅ መጠበባቸው የሚጀምረው "ረመዳን ደረሰ" መባል ሲጀምር ነው።

ልጅ እያለን ከጓደኞቼ ጋር ረመዳን ሲገባ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በህብረት በየጎረቤቱ እየዞርን እናዜማለን ፍራንክ እንቀበላለን። ታዲያ ሀራሪስቶች በዚህ ድርጊታችን አይደሰቱም። ፆሙ ለነሱ የግዞት እስር ቤት ስለነበር እንኳን አደረሳችሁ ለነሱ ስድብ ነው። ይሄ ዜማችን በእናቶቻችን ዘንድ ሳንቲምና ምርቃት ሲያስገኝልን። በሀራሪስቶች "ኢንአል አቡክ!!ውጡ ምድረ ዲቃላ! የሚል ዘለፋ ያስገኝልናን።

ረመዳን ሱሴዎች ላይ በሚፈጥረው ተፅዕኖ የረመዳን ፆም ከየትኛውም የመርካቶ ክፍል በተለየ እኛ ሰፈርና ዙሪያ ገቡ ላይ ያይላል። ምክኒያቱም ከላይ እንደተገለፀው አብዛኛው የሰፈሬው ወጣት ታታሪነ ቃሚ ነው። ከጫት ጋር ተለይቶ መዋል ከውሃውስጥ እንዳወጧት አሳ ያንቸፈችፈዋል። ድሮ ነው ታዲያ።ዛሬ ላይ ያን ሁኔታ ደግሞ ማየት የሚፈልግ ካለ… ይሂድ መሳለሚያ 01 ቀበሌ ሰፈር ። የድሮ ሰፈሬን የረመዳን ድባብ ቅልብጭ አድርጎ ያስቃኘዋለል ።"የዛ ሰፈር ሰው ለጫት ያለው ፍቅር ለሀገሩ ቢሆን ኖሮዛሬ ከነ ቻይና እኩል እንበለፅግ ነበር ይላሉ የሰፈሬ ነገረኛ ሴቶች በቡና ሰዐታቸው ሰፈሬን ሲያሙት"

  በዚህ ነው የረመዳን ወር ሰፈሬ ላይ በግልፅ ጫናው እስኪታይ ድረስ ያይል የነበረው። እስኪ አስቡት ጎህቀዶ ጎህ እስኪሰፋ ማመንዠግ የለመደ አፍ መመርቀንየለመደ አይምሮ ለአስራ ምናምን ሰዓት ከነዚህ ነገሮች ታቅቦ ሲውል ምን ሊፈጥር እንደሚችል አስቡት። የሰፈሬ ቃሚዎች ለምን የረመዳን ፆም እንደሚበረታባቸውገባቹ አይደል? ለምሳሌ:- አንድ የኔ ቢጤ ሀራሪስቶቹን ምፅዋት ቢጠይቅ በትንሹ ግልምጫ አለፍ ካለም እርግጫ የግሉ ነው። ሰዓት የጠየቀማ አለቀለት። ያስተውሳቸላ አይሬውን!! ከወሩ ክፍል በሀራሪስቶች ዘንድ እጅግ የሚናፈቅ ነገር ቢኖር የመግሪብ የሰላት አዛን ነው። ምክኒያቱም ፆም (የማፍጠር) የመግደፍ ብስራት ስለሆነ። ብዙውን ጊዜ ፆም የሚገድፉ ሀራሪስቶች ለማፍጥር አምስት አስር ደቂቃ ሲቀር ሲጋራና ክብሪት ያዘጋጃሉ፣ ወይም ደግሞ ትኩሱን ሾርባ እያቀዘቀዙ አዛኑን ጆሯቸውን ቀስረው ይጠብቃሉ። ልክ ይሄ አዛን ሲሰማ የሚፈጠረው የደስታ ጩኸት የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቡድን ጎል ሲያገባ የሚፈጠረው አይነት የደስታ ጩኸት ጋር ሲጋራውንም ሾርባውንም በአንድ ትንፋሽ ሂድ በለው…!!

  የሰፈሬ የረመዳን የምሽቱ ድባብ ደግሞ ከየ አቅጣጫው በሚሰማው የተረዊህ ድምፅ ሳውንድ ትራክ ታጅቦ እዚህም እዛም በየበረንዳው ላይ በሞቀ ሁኔታ ተፈርሾ፣ እጣን ሲጨስ፣ ትኩስ ነገር ላይ በላይ ሲቀዳ… ጥምጣምና ሻል ባደረጉ ወጣቶች ሲቃም የሱዳን ዜማ ተከፍቶ… ቀን በሀራራ ሲቧጨቅ የዋለው ማህበረ ሰብ ፍቅር በፍቅር ሆኖ ይታያል። ።ይህ ድባብ  ከመለኮታዊ ትዕዛዝ ያፈነገጠ ቢሆንም ከአይምሮ የማይጠፋ ትውስታዬ ሆኗል። ዛሬ ቅዝቅዝ ቢልም ሲኒማ ራስ አካባቢ ጣፈጭ ብሱኩቶች፣ኩሬይባት፣ ሙሸበክ፣ ሳንቡሳ፣ ቴምር… የሚሸጥበት ስፍራ የነበረው የረመዳን ምሽት ገፅታ ራሱ ረመዳንን የሚያስናፍቅ ነበር። ከትውስታው አንድ ሁለት ሶስት አስቂኝ ገጠመኝ ልጨምር…

• በፆሙ የመጨረሻ ሳምንት በጎረቤቶች የሚዘጋጅ ሰደቃላይ  ነው። በዚህ ሰደቃ ከጎረቤቶች ጀምሮ እስከ የኔ ቢጤዎች ታድመውበታል። የኔ ቢጤዎችን (ደረሳዎች) እያስተናገድኩ ቆየው… በዚህ ሂደት አንዱ የኔ ቢጤ አበላሉ ሲመሰጠኝ

<<ይሄ ደረሳ ሆዱ ውስጥ ሌላ ፌስታል የያዘ ደረሳ ሳይኖር አይቀርም>> አልኩና ላይ በላይ ትልልቅ ስጋና አጥንት አቀረብኩለት። ጀለሴ አቅሉን እስኪስት በልቶ በልቶ ያመሰግነኛል ብዬ ስጠብቅ…

<<ምነው ቢላ የላችሁም እንዴ?>> አይለኝም መሰላቹ? በጣም አናዶኝ አረ እናትን… ብዬ ድንጋይ አንስቼ መሃል አናቱ ላይ ልለው አሰብኩና" ይሄ ከአላህ መንገድ የሚያወጣ"በሚል ዛቻ አለፍኩት።

• የመግሪብን ሰላት እዛው ሰፈር ጎዳና ላይ ህብረት ፈጥረን በእንሰግድ ነበር። ታዲያ የመግሪብ ሰላት ከጄት በፈጠነ ፍጥነት ጠቅ… ጠቅ… ጠቅ…ተደርጋ ከመጀመሯ ትጠናቀቃለች። አሰጋጁ ትንሽ ረጋ ብሎ ያሰገደ ከሆነ ሰላቱ ሲያልቅ እሱን አያርገኝ። ለዚህም በሚል አሰጋጁ ፈጠን ፈጠን እያደረገ ለማሰገድ ይገደድ ነበር። 

አንድ ቀን ይህን ሰላት ለመስገድ የሰፈር ልጆች ተሰባስበናል። አጠገቤ ሳያጨስ ለመስገድ የቆመ ሀራሪስት ቆሟል። አንድ ሰው ማሰገድ ጀመረ። ሁላችንም ሰላታችንን እሱን ተከትለን ቆምን።

ኢመሚ ፋቲሃን ቀራ… ወለዷሊን…

አአአአአሚሚሚሚ ሚን… አልን በጀመዓ። … ቀጠለ ረዘዘዘዘም ያለ ሱራ መቅራት ጀመረ … አጠገቤ የቆመው ሀራሪስት ይህ የኢማሙ ሁኔታ አናደደው። ቢጠብቅ ሩኩዑ አይወርድም… ቢጠብቅ ሩኩዑ አይወርድም… ንዴቱ አናቱ ላይ ወጣ… ሰላቱን መቀጠል ተሳነው…

ሰላቱን አቋርጦ ያጣመረው  እጁን አያወናጨፈ <<ይሄ ህፃን ሆነ እንዴ? እናቱን ልብ**>> ብሎ ቃሉን ሳይጨርስ ኢማሙ ሩኩዕ ወረደ። ሀራሪስቱም ንዴቱ በርዶለት ምንም እንዳልተፈጠረ ነገር ሰላቱን ቀጠለው… አላህ ይቅር ይበለን።

• ከዚህ ከመግሪብ ሰላት ጋር ተያይዞም አንድ ቀን ከሀራሪስት የሰፈሬ ሰዎች አንዱ ያሰግደን ዘንድ ኢማም አደረግነው ። የመጨረሻውተሽሁድ ላይ ተቀምጠን " አጠገባችን መኪናና መኪና ከባድ ግጭት ተጋጩ ያሰግደን የነበረው ሰው ሳያስበው በድንጋጤ <<በለው>> ብሎ ጮኸ። ጆሮዬን አላመንኩም። አጠገቤ ያለ ሰጋጅ,,,ህዕ,,,ብሎ ለመሳቅ ሲቃጣው እኔም አላስቻለኝም። ይህንንና መሰል ክስተቶች በረመዳን ወር ያይሉ ነበር። (አላህ ይዘንልንና)።

ዛሬ ላይ ግን ይህንና መሰል ሁኔታ የለም ማለት ይቻላል። ወጣቱ ነቅቷል አልሀምዱሊላህ። በእነዚህና በመሰል ክስተቶች መማርና ረመዳናችን እንዳይበላሽ መጠንቀቅ ይኖርብናል።
እንደሚታወቀው ይህ ታላቅ ወር ደርሷል በተቻለን አቅም በዚህ ወር ትሩፋቶች ለመጠቀም ካለፈው ጊዜ ጠቀሜታ አልባ ከበርቻቻ ታቅበን ልናሳልፈው ይገባል። አላህም ያግዘን።

No comments:

Post a Comment