Saturday, August 20, 2016

አይ መርካቶ

አይ መርካቶ!

አገር ከየጎራው ወጥቶ
አንቺን ብሎ ነቅሎ መጥቶ
ግሣንግሱኘሡን ጓዙን ሞልቶ
ኅልቄ መሣፍርትሽ ፈልቶ
ባንቺ ባዝኖ ተንከራቶ
እንደባዘቶ ተባዝቶ
ተንጠራውዞ ዋትቶ ዋትቶ

አይ መርካቶ!

የምድር ዓለም የእንጀራ እናት
ላንዱ ርካሽ ለሌላው እሣት
ላንዱ ፍትሃት ላንዱ ምትሃት
ላንዱ ሲሳይ ላንዱ ፍርሃት
ላንዱ ተስፋ ላንዱ ስጋት
የግርግር የሆይታ ቋት

አይ መርካቶ!

ያንዱን ወስዶ ላንዱ ሰጥቶ
ያንዱን ገፍፎ ላንዱ አብልቶ
አንዱን ነስቶ ላንዱ አድልቶ
ስንቱን ፈርቶ ስንቱን ሸሽቶ
ባፈ ጮሌ ተሸልቶ

እይ መርካቶ!

ቢያዋጣ ወይ ባይዋጣ
ከስንቱ ተንጣጥቶ ጣጣ
ተነታርኮ ተገዛግዞ
ተብለጥልጦ ተበዛብዞ

መርካቶ ያገር ድግሱ
የገጠር ስንቅ አግበስብሱ
ለከተሜው ለአባ ከርሱ
በትሬንታው በአውቶብሱ
በቁሳቁስ ግሳንግሱ
ለቱጃር የጥጋብ ቅርሱ
ለኔ ቢጤው የቀን ጉርሱ
አባ መስጠት እጦት ቢሱ

አይ መርካቶ!

ተሻምቶ ተገበያይቶ
ወይ ተፈራርሶ ተጣልቶ
በእንካ ስላንቲያ ተማትቶ
አንዳንዴም ተፈነካክቶ
ተመራርቆ ተስማምቶ

አይ መርካቶ!

የኤስፔራንቶ ቋንቋ ሀገር
ያ ሲነገር ያ ሲሰበር
የስንቱ ልሳን ሲቀመር
ያንዱን ሲያከር ያንዱን ሲያቀር
ያንዱን ሲያውስ ያንዱን ሲያስቀር
ያ ሲደቀል ያ ሲፈጠር
የልሣን ሸማች ለብቻ
ከዕቃው ጭምር በስልቻ
ሲመዠርጥ እንደ ግቻ
ቶሎ በል ቶሎ በል ብቻ
ዝግ በሉ እማይባልበት
መርካቶ የአንደበት ፍላት
ግርግር እሚባልባት
ክርክር እሚሞቅባት
ደላላ እሚያውጅባት
ቸርቻሪ እሚተምባት
ሌባ ላብክን እሚያልብባት

አይ መርካቶ!

ላንዱ ምድር ላንዱ ጣራ
ያ ሲዘረፍ ያ ሲደራ
ያ ሲወስን ያ ሲፈራ
ያ ሲሸሽግ ያ ሲያወራ
የንግድ ጠፍ ወይ ያዝመራ
የነጋዴ ምጥ መከራ
የከበረ እንደመረዋ፣ረብጣ አፍኖት ሲያስገመገም
የከሰረ እንደ ፈላስፋ፣ በቁም ቅዠት ሲያልጎመጉም
የኔ ቢጤም ጠብሻ መቶት፣በየጥሻው ሲያስለመልም
ቸርቻሪ ዝርዝሩን ቋጥሮ፣ቅንጣቢውን ሲቃርም
የወር ሸማች ስንቁን ጭኖ፣ ሲመርቅና ሲረግም
ማጅራት መቺ ከጀርባው፣ ጥሻውን ዘሎ ሲያዘግም
ከዚህ በርሮ እዚያ ሰብሮ፣ ያዝ ሲባል ሲሸሽ ሲጣጣር ካማኑኤል ከራጉኤል፣ ሾልኮ ዶሮ ማነቂያ ዳር ከመስጊድ እስከበረንዳ፣ ከአራተኛ እስከ ነፍስይማር
የኡኡታው የጡሩንባው፣የጩኸቱ የፊሽካው ሳግ
የሰው የመኪና የከብት፣ የፍግ የቁሳቁስ ትንፋግ
ሲገፋተር ሲገሻለጥ፣ ላቦት ለላቦት ሲላላግ
ትንፋሽ ለትንፋሽ ሲማማግ
አባ ሽብሩ መርካቶ፣ ያለውን አጣጥቶ
የሌለውን ከሌለበት፣ እስጎልጉሎ አስወጥቶ
ስንቱን ከዳር ዳር አዛምቶ
በግድም በውድ አስማምቶ
አገር ካገር አካቶ
ሁሉን አቀፍ ባይ መርካቶ
ያቻችለዋል አሻምቶ
አይ መርካቶ!

ከክቡር ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን

No comments:

Post a Comment