Wednesday, April 5, 2017

ለውጡ

"ለ     ው     ጡ"
#ሳteናw

  ግማሽ እፍኝ የሚሆነውን የላይ አባዲር ት/ቤት ትውስታዬን፣ በታች አባድሩ ፅሁፌ፣ እንደምቸከችከው ቃል የገባሁ ቢሆንም ቅሉ፣ ከጉዳዩ ኢ–አሳሳቢነትና ከነሻጣ ማነስና አንፃር ሳልፅፈው እስከዛሬ ዘግይቻለው። ዛሬ ግን በአንዲት የማህበራዊ ድረገፅ ወዳጄ አነሳሽበት፣ የቻልኩትን ያህል ልቸከችከው ነሸጥኩ።

    ከዜሮ ክፍል አስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ከሚያስተምረው ታች አባዲር ስድስተኛ ክፍልን በአንዳች ተዓምር አልፌ፣ በመቶ ሜትር(radius) ክልል ውስጥ ወደ ሚገኘው (ሌላኛው ቅርንጫፍ) ላይ አባድር ሰባተኛ ክፍል ስገባ ከታችኛው አባድር አንፃር ብዙ ለውጦች መታዘብ ቻልኩ። ልዩነቱ የጀመረው ገና ከአጥር በሩ ነበር። … ልሙጥ ቆርቆሮ በሞራሌ ስሪት የነበረው የታች አባድሩ ዋና በር፣ በላይኛው አባድር በዛሬ ዘመን ተጠፍጥፎ "ሁለት ሲኖትራክ ሊወጣው ይችላል" ብለህ ለመከራከር የሚያበቃህ ወፍራምና አጭር ብረት በር ሆኖ ተገኘ። ሲቀጥል ከበሩ አቅራቢያ ሁሌም ተሰይመው በሚገኙት ጥበቃዎች ጋሽ ሲራጅና ጋሽ ፀጋዬ(ስማቸውን ከተሳሳትኩ አርሙኝ) መካከል የነበረው ልዩነት ሆነ።  በተፈጥሮ ወጣ ወጣ ብለው በበቀሉ ጥርሳቸው ሳቢያ፣ ሁሌም የሚስቁ ከሚመስሉት ከታች አባድሩ ጥበቃ ጋሽ ስራጅ ሁሌም ከበሩ የሚቀበለን የፈገገ ገፅታ በተቃራኒ፣ ከነጭ ጎፈሬ ፂማቸው ጋር ቀይ በቀይ ቢለብሱ የገና አባት የሚመስሉትና እጅግ ሲሪየስ ገፅታ ባላቸው በላይ አባድሩ ጥበቃ ጋሽ ፀጋዬ፣ ሁሌም በማይፈታ ገፅታ  ተተካ። በት/ቤቱ በነበረኝ ቆይታ ጋሽ ፀጋዬ አይደለም ሲስቁ፣ ሲያወሩ እንኳ ጥርሳቸውን አይቼው አላውቅም ብል ግነት አይደለም። ምናልባት ጥርሳቸውን ገጥመው ያወሩ ይሆናል። ታዲያ ዛሬ ላይ ሆኜ የሁለቱ ጥበቃዎች ልዩነት ሳጤን!! አይ ተፈጥሮ እንደው ስታዳላ! ያስብለኛል። እዚህ ጋር ጥበቃው ጋሽ ፀጋዬ ከተማሪው ጋር የሚያገናኛቸው ተግባር ታወሰኝ። ዘወትር ትከሻቸው ላይ በማይታጣውና፣ እንደ አንዳች ነገር በሚጮኸው ጅራፋቸው፣… ወንጭፉን እያወናጨፈ ከማሽላው ማሳ ላይ እዋፋትን እንደሚያባር እረኛ፣ የአስቸጋሪ ተማሪዎችን ስብስብ በጅራፉ ጩኽት በማስደንበር የሚያባርሩትም ደርጊታቸው ከግማሽ አፍኝ ትውስታዬ ውስጥ የራሱን ድርሻ ይይዛል።

ሌላው ለውጥ ደውሎቹ ነበሩ።  በጋሽ ስራጅ አጋፋሪነት ብረትን ከብረት አጋጭቶ በሚፈጠር ድምፅ የነበረው የት/ቤቱ ደወል፣ እንደ ድሮ ስልክ ጢርርርር ወደሚል በኤሌክትሪክ ደወል ተለወጠ። ከባህላዊነት ወደ ዘመናዊነት የተደረገ ሽግግር! ብለህ ፈርጀው። ታዲያ መብራት ሲሄድ ደወል የሚበሰረው በጋሽ ፀጋዬ የጅራፍ ጩኸት ነበር !! ብዬ ብቀልድ ሀቅ እንዳይመስልህ Lol። እንደሻማ ነበልባል በትንሽ ትንፋሽ ይርገበገቡ የነበሩት የታችኛው አባድር  የመማሪያ ክፍል በሮች፣በድማሚት እንጂ በሌላ ሀይል የማይበገር በሚመስል በወፍራም የእንጨት በሮች ሆኖ በላይ አባድር አየው፣ በቀለም አልባ ቦሎኬት ግድግዳና ኢ_መስታወት በሆነ መስኮት የተማርኩበት የታች አባድሩ የነኮቱ የመማሪያ ክፍል፣ በድጋያማና ውስጣዊ ክፍላቸው በቀለም በደመቁ ክፍሎች፣ በከፊልም ቢሆን ባለመስታወት መስኮቶች ያሉት ሆኖ አገኘሁት። እንደ ወንፊት በተበሳሳው ቆርቆሮ ቀዳዳ ውስጥ ሾልከው ደብተሬ ላይ የሚለጠፉ ጨረሮች፣ (እጫወትባቸው ነበር)፣ እድሜ ኮርኒስ ለተባለ ቴክኖሎጂ በላይኛው አባድር አልነበሩም።  የሁለቱ አባድሮች የመማሪያ ዴስኮችም ቢሆኑ አራንባ ቆቦ ነበሩ። ገና ተማሪው ሲቀመጥባቸው፣ እያረገረጉና በሲቃ እያቃሰቱ ከረባሽ ተማሪዎች ይበልጥ፣ (የመምህር ፍራቻ ሳያግዳቸው) ክፍሉን ይረብሹ ከነበሩት ከታቹ አባድር፣ የተሻሉ ጠንካሮች ነበሩ። ምናልባት የት/ቤቱ አስተዳደር የተማሪው እድሜና ክብደት ላይ አባዲር ሲገባ እንደሚጨምር ስለተረዱ ይሆናል ይህን ሁሉ ለውጥ በላይ አባድሩ ያበጁት። በአጠቃላይ የታች አባድር ክፍሎችና የላይኛው ልዩነታቸው በሳሎን ቤትና በማዕድ ቤት እንዳለው አይነት ነበር። እናም ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል በኩሽና ብማርም ሰባትን በሳሎን ተማርኩ ብዬ ብዘባባት እንዳትፈርድብኝ።

ላይ አባዳር ከታች አባድሩ አንሶ የሚገኘው፣ በክፍሎች፣በመፀዳጃ ቤቶች ብዛት፣እና በቅጥር ግቢው ስፋት ነበረ። የላይ አባዲር ጊቢ ከጥበቱ የተነሳ፣ የአንድ ክፍል ተማሪዎች እንኳ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማሰራት የማይመች ነበት። በአካል ብቃት እንቅስቃሴው ሂደት፣ በመምህር መሀመድ ሱልጣን ፊሽካ እየተመራን እጃችን ስናጥፍ ስንዘረጋ፣ እጃችን በየክፍሎቹ መስኮት ይሾልኩ ነበር ብል እያጋነነኩ ቢሆንም፣ ከመጠን በላይ ጠባብ መሆኑ፣ያፈራቸው ተማሪዎች ምድክር ናቸው።

ለውጡ በት/ቤቶቹ ይዘት ብቻ አልነበረም። በትምህርት አይነቶችም ጭምር እንጂ።በመምህር ኤሊያስ የተማርኩት ኢትዮጲያዊው የሂሳብ ትምህርት፣ ዜግነቱን ቀይሮ "maths" ሆነ። በመምህር ኑር ሁሴን የተማሩኩት ሳይንስ፣ ባይሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ ተብሎ እንደ እንትን ሶስትም አንድም ሆኖ ተገኘ። ለሀገሬ የነበረኝ ፍቅር ወደር ስላልነበረው፣ ዜግነት የለወጡ ትምህርቶች ልክ እንደ ሶላቶና ባንዳ ስለምመለከታቸው፣ የተግባባንበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። ለነገሩ የሚገባኝና በጣም ጥሩ የተሰኘ ነጥብ ማስመዘግብበት የትምህርት አይነት ቢኖር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተግባር ላይ ነበር።

… በአንድ የት/ ክፍል የስፖርት አስተማሪያችን የነበረው መሀመድ ሱልጣን፣ የመጀመሪያ የወር አበባ ማየቷ አስደንግጧት፣ ከቤቷ ኮብልላ ስለጠፋች ልጅ አገረድ፣ ትራጄዲ ታሪክ ሲተርክልን… እንዴ ከምኔው ከስፖርት አስተማሪነት፣ወደ ታሪክ አስተማሪነት ተከረባበተ ብዬ የተገረምኩበት… ገጠመኝ ሌላኛው ትውስታ ነው።

ጋሽ በቀለ በሚባል የጎማ አለንጋ፣ የእጃችን አንጓ እስኪናጋ ድረስ ይገርፈን የነበረው ኡስታዝ ፉዓድ በኛ ጊዜ፣ ዩኒት ሊደር ነበር(መሰለኝ)። ተማሪው ለሱ የነበረው ፍራቻ ከፍተኛ ነበር። የሱን መምጣት የምናውቀው፣ ጠብደሉን የቅጥር ጊቢውን ብረት በር፣ እያንገጫገጨ በሚንኳኳው ድምፅ ነበር። በዚህ ጊዜ በስድስቱም ክፍል ያለ ተማሪ፣ በመምህሩ ፍራቻ ሽንቱ ባያመልጠው ይመጣ ይመስለኝ ነበር።

ባይሎጁ መምህር ባልሳሳት ቲቸር ፀጋዬ፣ በአንድ የትምህርት ክፍለ ጊዜ፣ ስለ ሲጋራ መጥፎነት፣ ሲያተምሩን፣ በአባታዊ ምክር "አደራ ልጆቼ ሲጋራ፣ በምንም መልኩ እንዳትለምዱ"እያሉ በራሳቸው ህይወት ላይ የፈጠረውን ተፅዕኖ እንደምሳሌ እየገለፁ ብለው የመከሩን መቼም አይረሳኝም" ዛሬ በህይወት የሌሉት የእኚሁ መምህር ምክር (ነብስ ይማር)፣ አብረውን ከተማሩ ውስጥ አጫሾችን ሳይ፣ ምክራቸው በከፊል መምከኑን ታዝቤያለው። በላይ አባድር የነበረኝ ቆይታ የአንድ አመት ብቻ በመሆኑ ከዚህ በላይ ትውስታዬን ወደ ቃላት፣ ሀረግና ዓረፍተነገር (convert) ማድረግ አልቻልኩምና በዚሁ ልንካው።

ወገሬት!!

No comments:

Post a Comment